«ልጆቼ ሆይ ስሙኝ!» የምላችሁ እናታችሁ ኢትዮጵያ ነኝ። እንደምታዩኝ በአላት በመጡ ቁጥር በእናንተ በልጆቼ አማካይነት ደስተኛ ለመሆን እሞክራለሁ። በአሁን ጊዜ በአላትን የማከብረው ቄጤማ ጎዝጉዤ፣ ዶሮና በግ አርጄ፣ ጠላና ጠጅ ጠምቄ፣ ቤቴን በአረቄ አሽትቼ ለማክበር አቅሜ እየተፈታተነኝ ነው። ፀዓዳ ለብሼ፣ በጥበብ አጊጬ፣ የተስፋ ስንቅ ይዤ በአላትን ከልጆቼ ጋር ሳከብር ብዙዎች አቅም አ‘ተው ሲቸገሩ ስመለከት ውስጤን ይጨንቀዋል።
የደንቡን የባህሉን እንዳያጡ ብዬ የማላደርገው ነገር የለም። የእኔነቴ ምልክትቶች ደብዛቸው እንዳይጠፉ፣ እምነቴ እንዳይናጋ፣ ባህሌ ወጌና ቅርሴ ተንቆ እንዳይቀር የደላኝ መስዬ ከልጆቼ ጋር ሳከብር የሞላልኝ የሚመስላቼው ብዙዎች ናቸው።
ዛሬ ብዙዎቹ ልጆቼ በግና ዶሮ ማረድ፣ ጠላ መጥመቅና ፀዓዳ መልበስ እያቃታቼው ብሩን ይዘው «እማ! ይቺን ለስንቱ ላብቃቃት?» ሲሉኝ የማደርገው ሁሉ ይጠፋኛል። የብዙዎች የተከፋ ፊት፣ «እማማ ለምን ተፈጠርን?» የሚሉ የሶቆቃ ድምፆችና መራራ ሞት ለመወበል በረሃ አቋርጠው፣ በባህር ተሻግረው ስደት ላይ የሚገኙ ልጆቼ በርክተዋል። እንሆ ዛሬ ድምፄን የማሰማው ከድህነት፣ ከእርዛትና ከሞት መንገድ ወጥተን በሰላም፣ በፍቅርና በብልፅግና መንገድ እንድንጓዝ ነው።
ልጆቼ ልብ በላችሁ አድምጡኝ! እኔ እናታችሁ ኢትዮጵያ ጥንት የነዚያ ጀግኖች እናት ነበርኩ፣ አሁን የእናንተ እናት ሆኜ አለሁ፣ ወደፊት ደግሞ የልጆቻችሁ እናት ሆኜ እኖራለሁ። የአኗኗሬ ጉዳይ ግን ጥያቄና ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ሆኗል። የእውነት! ውበት ሳላጣ ተንቄ፣ ጉልበት ሳላጣ ተኮራምቼ መታየቴ ዓለምን የሚያወያይ አሳዛኝ እንቆቅልሽ ሆኗል። ሁልጊዜ «ለምን እንዲህ ሆነ?» ብዬ እጠይቃለሁ። የዳቦ ቅርጫት ተብዬ ልጆቼን በየዓመቱ የምግብ እጥረት ሲያጋጥማቼው ውስጤ ይደማል። ደንበር አቋርጦ የሚፈስ ውሃ እያለኝ ልጆቼ ውሃ ሲጠሙ መላ አንጀቴ ይቃጠላል። ለምለም አፈርና ተስማሚ አየር ባለቤት ሆኜ ዘወትር ለልመና እጄን ከኔ በኋላ ለተፈጠሩት ምዕራባዉያን ስዘረጋ አንገቴን ደፍቼ አለቅሳለሁ። ውብና አኩሪ ወንዞቼ፣ ተራሮቼ፣ ደኖቼ የባዕድ ምኞት መፈንጫ ሆነው ስመለከት የበለጠ እበግናለሁ። ይሄ ሁሉ ሲሆን ጥያቄው የሚወረወረው ወደ ልጆቼ ነው። መልሱም የሚገኜው ከልጆቼ ነው። እኔም መልዕክቴን የማስተላልፈው «እማማ!» ብለው ለሚጠሩኝ ለልጆቼ ነው። እናትነቴን አምናችሁ ልጅነታችሁን የተቀበላችሁ፣ በቅርብም በርቀትም ያላችሁ፣ በድሎትም ሆነ በእጦት ያልተለወጣችሁ ሁሉ መልዕክቴን ልብ ብላችሁ አድምጡኝ።
ልጆቼ ሆይ! በመጀመሪያ ደረጃ ከሁሉም በፊት መጥፎ የሆነ አስተሳሰብን፣ ምቀኝነትን፣ ቅናትን ከዉስጣችሁ እንድታስወግዱልኝ እማፀናችኋለሁ። እነዚህን ሰይጣናዊ አስተሳሰቦች በውስጣችሁ ይዛችሁ እኔንም ልታደምጡ እርስ በእርስም ልትደማመጡ አትችሉም። መጥፎ አስተሳሰቦች መጨረሻቸው ውድቀትን ነው የሚያፋጥኑት። ይህም ብቻ ሳይሆን ጆሮን ደፍኖ፣ ልብን በትዕቢት አሳብጦ፣ ሰብአዊ ስሜትን አናግቶ እያጨራረሰ ወደ እሳት ይጨምራል፣ ወደ ገደል ይገፈትራል። ከጥንት ጀምሮ የውጭ ወራሪዎች የምቀኝነት የዕብሪት ጦርነት ሳያንሰኝ የእናንተ የልጆቼ የእርስ በርስ አለመግባባት ሲያቆስለኝ፣ ሲያደማኝና ሲያሰቃዬኝ ኖሯል። የድህነቴ ዋነኛ ምክንያትም የቀና አስተሳሰብ ጉዳይ ነው። የልጆቼ የእርስ በርስ ሰላም ማጣትም ለእድገቴ ትልቅ ጸር ሆኖብኛል። እንዲህ አይነቱ ወደ አዘቅት የሚጨምሩ መጥፎ አስተሳሰቦችን አሁን ይብቃ ነው የምለው።
«ልጆቼ ሆይ ስሙኝ!» የምላችሁ እናታችሁ ኢትዮጵያ የአዲስ ሕይወት ምዕራፍ ከፍታችሁ ሁላችሁም ቂማችሁን ከልባችሁ አውጥታችሁ ታረቁ እላለሁ።
በአዲስ የአስተሳሰብ ፀበልም እንድትጠመቁ እጠይቃችኋለሁ። ከኋላ ያለፋችሁበት ታሪክና መንገድ ለአሁን ፍቅርና ሕብረት የሚረዳ ስለሆነ ዘወር ብላችሁ ታሪካችሁን ተመልከቱት። እናት አባትን ማክበር፣ ለእህት ወንድም መታዘዝ፣ መልካም ነገርን ማድረግ፣ ውብ ባህሎችን መጠበቅ የእናንተ የልጆቼ መለያ መሆን አለበት። ብዙ ወደ ኋላ መመልከት የወደፊት ጉዟችሁን የተቃና ስለሚያደርገው ታሪኮቻችሁን መዘንጋት የለባችሁም። ለአንድ አፍታ አንገታችሁን ዘወር አድርጋችሁ ታሪካችሁን ተመልከቱ። በተለያዬ ጊዜ በልጆቼ መሐል በየጊዜውና በየወቅቱ ትንሽም ሆነ ትልቅ ፀብ ይፈጠራል። ፀቡ ግን ወዲያው የሚፈታ እንጂ ጥርስ የሚያስነክስ ቂም አርግዞ የሚኖር መሆን የለበትም። ይህ ለውጭ ተመልካቾች ትዝብት ከመመቸቱም ሌላ ውስጣዊ ድክመትን አስከትሎ መውደቅና መበታተንን ያመጣል። ያኔ ለባዕድ እጅ መግቢያ ቀዳዳ ከፈታችሁ ማለት ነው። ከዚህ ድርጊት አደራችሁን ተጠንቀቁ።
እኔን እናታችሁን ገፍታችሁ አዋርዳችሁና ክብሬን አስነጥቃችሁ፣ ባዕድ እጅ ላይ ወድቃችሁ፣ በሞግዚት እንዳትተዳደሩ እፈራለሁ። የባዕድ አገዛዝ እውነቱን ልንገራችሁ ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን አስታውሱ። ለልጆቼ ቅን አሳቢ መስሎ ለሁለተኛ ጊዜ መሬቴን የረገጠው ጣሊያን የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ·ም በልጆቼ ላይ ያደረሰው እልቂት መቸም ቢሆን ከሆዴ የሚወጣልኝ አይደለም። ስለሆነም የእኔ የእናታችሁ ውበትና ሀብት የባዕድ መደበቂያና መፈንጫ እንዳይሆን በአንድነት ጠንክሮ የመጠበቁ ኃላፊነት የወደቀው እናንተው ልጆቼ ላይ ነው።
ልጆቼ! አመላችሁ ሁሉ ልውጥውጥ ብሎብኛል። ባህላችሁን እረስታችሁ በምዕራባውያን ባህል ተተብትባችሁ ከኔ ከእናታችሁ ታሪክ ይልቅ ለውጩ ምናችሁም ላልሆነው ስትጨነቁ ስመለከት ትልቅ ችግር ላይ እንዳላችሁ ተረድቻለሁ።
ለመሆኑ እንደዚህ አይነት የባህል፣ የማንነት ወረርሽኝ ላይ ያደረሳችሁ ነገር ምንድነው?
የዘመኑ አዳዲስ መሳሪያ? ጥቅም? ምኞት? ቋንቋ? ወይስ ሌላ? እስቲ ራሳችሁን በቅጡ መርምሩት።
ልጆቼ፣ ከባህል ማፈንገጥ ለማንም አይጠቅምም። ለዚያውም የኔን የእናታችሁን ውብ ባህል እንደምንም በመቁጠር ከኔ በኋላ ለተፈጠረው ነጭ ማጎብደዳችሁ በጣሙን ነው ያሳዘነኝ።
የምዕራባዊነት ምኞት ለውድቀት ማራመጃ የሚውል ብቻ ሳይሆን ለአስተሳሰብ ብክነትም የሚዳርግ ነው።
ታላቅ የሕዝብ አደራ መሆኑን ብታውቁ ባህል ማክበር እንቅልፍ የሚነሳ ሸክም ነው።
«ልጆቼ ሆይ ስሙኝ!» የምላችሁ እናታችሁ ኢትዮጵያ አንድ ነገር ልምከራችሁ። እኔ እናታችሁ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት አለኝ። ነገር ግን ይህን ሀብቴን በአግባቡ አልተጠቀማችሁበትም። እውነቱን ልንገራችሁ፣ ጠንካራ ሠራተኛ ካገኘሁ፣ ሁላችሁንም የሚጠቅምና የሚያዝናና በቂ የሀብት ክምችት አለኝ። ከተማ መከተሙን ትታችሁ ወደ ገጠር ወረድ ብትሉ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ታገኛላችሁ።
ለማንኛውም ግን በርቱልኝ፣ ተስፋዎቼ እናንተ ናችሁና ጠንክሩልኝ። ከቅርብ ግዚያት ወዲህ በቋንቋና ሀይማኖት ላይ የምሰማው ነገር «ልጆቼን ምን አገኘብኝ?» አስብሎኛል። በቋንቋና በሀይማኖት ልጆቼ ተጋጩ ሲባል አምርሬ ነው ያለቀስኩት። ልጆቼ! ቋንቋና ሀይማኖት በፍፁም ሊያጣላችሁ አይገባም። የሁላችሁን ቋንቋ የእኔው ቋንቋ ነው። የሁላችሁም ሀይማኖት የእኔው ሀይማኖት ነው።
የተለያዬ ቋንቋ መናገርና ለተለያዬ እምነት ማደር ሰብአዊ ወንድማማችነታችሁን ማናጋት የለበትም። ሁሉም ቋንቋዎችና ሀይማኖቶች መከበር አለባቸው። ሰው ራሱን እንደሚወድና እንደሚያከብር ሁሉ ሌላውንም ቢወድና ቢያክብር ወደዚህ ችግር አይገባም። የሌላውን የማይወድና የማያከብር ደግሞ በሌሎች ሊወደድና ሊከበርም አይችልም። ይህ ነው የፍቅርና የጥላቻ መሠረቱ። አሁን ያለፈው አልፏል፤ ከአሁን በኋላ ከልጆቼ የምፈልገው አዲስ የፍቅር፤ የመከባበርና የመተባበር ባህል ነው።
አሁን እውነተኛ ልጆቼን የምፈትንበት ጊዜ ላይ ደርሻለሁ። ሆዴ ባዶ ሆኖ ሁልጊዜ ለእርዳታ እጆቼን በዘረጋሁበት ወቅት በፖለቲካ የሚንጡኝን ምንም አይጠቅሙኝም። በቀደሙት ዘመናት በፖለቲካ ሰበብ ስታለብ ደም እንጂ ወተት አልሰጠሁም። አሁንም ደሜን ቢንጡት የደም ደም እንጂ ቅቤ አይወጣኝም። ወተት ለማግኘት መጀመሪያ ላሚቱን መንከባከብ ያስፈልጋል። የፖለቲካው ጨዋታ፤ የልጆቼ መሠረታዊ ፍላጎት ከተሟላና የእኔም ስም ከተመፅዋችነት መዝገብ ቃላት ከወጣ በኋላ ይደርሳል። ለዚያውም ፖለቲካ በብስለት የሚጫወቱት የአዕምሮ ጨዋታ መሆን አለበት። የስልጣኔና የሰልጣኖች መንገድ የሚያሳየን ይሄንኑ ነው።
የልጆቼን የጋራ ክንድ አጥብቄ ለልማት በምፈልግበት ወቅት በጎሳ፤ በሃይማኖትና በቋንቋ ሊከፋፍሉኝ የሚሞክሩትም የህልውና ፀሮቼ ናቸው። እኔነቴ የተግነባው በየአንዳንዳቸው ልጆቼ፤ ጎሳ፤ ሃይማኖት፤ ባህልና ቋንቋ ላይ ነው። አንዱን ከሌላው አብልጬ የማይበት ዓይንም ሆነ አንጀት የለኝም። ማዕዴን እኩል ተቋድሳችሁ፤ ፍቅሬን እኩል አፍቅራችሁ፤ ክብሬን እኩል አክብራችሁ በሕብረት መኖር ያቃታችሁ እናንተው ልጆቼ ናችሁ። ይህንንም የማይጠቅም መንገድ የማያሳዩአችሁ በውበቴ ተማርከው፤ በጥሬ ህብቴ ጎምዥተው ራሳቸውን ለሞግዚትነት ያዘጋጁ የውጭ ወራሪ ኃይሎችና ከእኔው ማህፀን የወጡ ጥቂት ጠባቦች ናቼው። ሙከራው፤ መልኩን ከመለዋወጡ በቀር፤ አዲስ አይደለም። ለብዙ ዘመናት በበርካታ ጊዜያት ከውስጥም ከውጭም እየተሞረ ያልተሳካ ሰይጣናዊ ህልም ነው። እግዚአብሔር ምንጊዜም ከእኔው ጋር በመሆኑ የልጆቼን መከፋፈል እንዳያሳየኝ እፀልያለሁ። ይህን የኋላ ቀር መንገድ እንዳትከተሉ ልጆቼን አደራ እላለሁ።
በመልኬ ብቻ እየኮሩ፤ ታሪኬን ደጋግመው እየዘመሩ፤ ምንም ሳይሰሩ እጃቼውን አጣጥፈው እያፌዙ የሚኖሩትም ምንም አይጠቅሙኝም። የጥንት ዝናዬ በጥንታዊነቱ የሚያቀርቡልኝ፤ እንቅፋት እንዳይመታኝ የሚጠብቁኝ፤ ውበቴ ረግፎ እንዳያልቅ የሚንከባከቡኝ የምመካባቸው ዓይኖች፤ ልቦችና እጆች ያስፈልጉኛል። ልባችሁ ለፍቅር፤ እጆቻችሁ ለስራ፤ እግሮቻችሁ ወደ ስራ ይነሱ።
ልጆቼ የትልቅ ታሪክ ባለቤት ሆናችሁ ወደኋላ በመቅረታችሁ በስልጣኔ የመጠቁትና በስራ የከበሩት ፈረንጆች ከርቀት ከረቫታቸውን እያስተካከሉ የፌዝ ሳቅ ይስቁባችኋል፤ የንቀት ርዳታቸውን የወረውሩላችኋል። ይህን ድርጊታቸውን አንድነታችሁን አጠናክራችሁ፤ በስራ ከብራችሁ ጥርሳቸውን አስከድኗቸው። እኔንም ከለማኝነት መዝግበ ቃላት አውጡኝ። ለእናንት ማን የመጣላችኋል? የውጭ የውጭውን አጨብጫቢ ሁሉ አትመኑት። <<አያድሩበት ቤት አያመሻሹበት ይባል የ!>> አጥፊዎቼም አልሚዎቼም እናንተው ልጆቼ ናችሁ። የጦርነት ተረትና ሙዚቃ ከእንግዲህ አያሻኝም። ጥፋት ይብቃ ለልማት ተነሱ። አሮጌ እድፋችሁን ተሸክማችሁ ወደፊት አትጓዙ። ገላችሁን በቅጡ ፈትጋችሁ ዕድፋችሁን ካስለቀቃችሁ፤ በአዲስ አስተሳሰብ የምትራመዱበት ቀና መንገድ፤ አዕምሯችሁና ጉልበታችሁን የምታውሉበት በርካታ የልማት ስራ ይኖራል። በከተማ የተከማቸው ጉልበትና አዕምሮ ወደ ገጠር ወጥቶ ይፍተን፤ ይቆፍር፤ ይመራመር፤ ያልተማረ ወንድሙን ያስተምር። የ እኔነቴ ውበት በከተማ ሕንፃዎች ላይ ብቻ ሊቆም አይችልም። የውበቴ መሰረቶች ገጠሩና ገበሬው ናቸው። ገጠሩ ይታረስ፤ ገበሬውም በስልጣኔ መብራት ይድመቅ። የከተማው ትርምስምስ በገጠሩ የጀርባ አጥንትነት ተደግፎ ትክክለኛ ግርማ ሞገሱን ያግኝ።
ዓለም በስልጣኔ እየገሰገሰች ነው። ስልጡን ሕብረተሰብም ለተራ ጭቅጭቅና ንትርክ ጊዜ እያጣ ነው። የስልጣኔው ውጤት ተጠቃሚ በሆነ ቁጥር ተፈጥሯዊም ሆነ ዘመን አመጣሽ ግጭቶቹን እያስወገደ በሕብረት ስልጣኔን መሞቅ ይዟል። ሠይጣኖችም በሰለጠነና በስራ ፍቅር በተጠመደ ሕብረተሰብ አዕምሮ ውስጥ የመግባት እድላቸው ጠባብ ነው። ስራ ፈት አዕምሮ ግን <<የሠይጣን መስሪያ ቤት ነው>> ይባላል። በባዶ ሆድ ንትርክ ትርፉ ድርቀት ነው። በስራ ተጠመዱ እኔንም በስልጣኔ ጎዳና ከሰለጠኑት ጎን አራምዱኝ። ይህንን ኋላ ቀር ትርምሳችሁን ትታችሁ፤ በብሩህ ተስፋ በፍቅርና በሕብረት በስልጣኔ የምታበሩበት ቀን እየናፈቀኝ ነው። ምክሬን ዛሬውኑ ጀምሩት። የጅምሩን ውጤት በቅርቡ እንደማየው ተስፋ አለኝ። ከእንግዲህ በእኔ በእናታችሁ ኩሩብኝ፤ እኔም በእናንተ በልጆቼ ልኩራባችሁ።
ሠላም፤ ጤና፤ ፍቅር ከእናንተው ጋር ይሁን። አሜን!!!!
=== አዲስ ፲፰፻፸፱ ===