February 22, 2014

የጠፈር ባይተዋሩ

‹‹የጠፈር ባይተዋሩ›› 
ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ።

ክፍል አንድ

‹‹ሞት እንደሁ ልሙት፣ በሴኮንድ መቶኛ 
እንቅልፍ እንደሬሣ፣ ዘለዓለም ልተኛ፡፡ 
… መንገድ ስጡኝ ሰፊ ስሄድ እኖራለሁ 
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ 
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ፡፡ 
የሌለ እስቲፈጠር የሞተ እስቲነቃ 
በትልቅ እርምጃ ከመሬት ጨረቃ
ከጨረቃ ኮከብ 
ካንዱ ዓለም ወዳንዱ 
ስጓዝ እፈጥናለሁ 
በፀሐይ ላይ ቤቴን ጎጆ እቀልሳለሁ፡፡
. . . መንገድ ስጡኝ ሰፊ 
ፀሐይ ልሁን ፀሐይ
እንደ ጽርሐ አርያም ሁሉንም የሚያሳይ 
እሳተ ገሞራ አመድ እረመጡን 
ጎርፍ የእሳት ጎርፍ ልሁን፡፡
… መንገድ ስጡኝ ሰፊ›› 
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበረው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ የ‹‹ጠፈር ባይተዋር›› ሲል በ1961 ዓ.ም ከገጠመው እጅግ ‘ሮማንቲክ’ እና ጥልቅ የጠቢብ መንፈሱን ከሚገልጽለት ቅኔው የተወሰደ ነው፡፡ 

ለማስታወስ ያህል- ሠዓሊና ባለቅኔው ገብረክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ህዋ ላይ በተለይ ‹‹አብስትራክት›› የተሰኘውን ዘመናዊ የሥዕል አሠራር ስልት በስፋት ከማስተዋወቅ በላይ የሀገሪቱን እና የሕዝቧን ሕይወት /ባመዛኙ አጽም በአጽም በሆኑ ሥዕሎቹ በመግለጽ፣ የጠቢብና የዜግነት ገዴታውን በመሥዋዕትነት ጭምር የተወጣ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ 


ድንቅ ሥዕሎቹንም በሀገርና በውጭ ሀገር በግልና በቡድን በተደጋጋሚ ያሳየ ሲሆን፣ በሕዝቦች የባሕል ልውውጥም በየጊዜው የኢትዮጵያ የሥነጥበባት ቡድን መሪ ልዑክ በመሆንም በልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ አደባባዮች ላይ ሀገሩን የወከለ የጥበብ ሰው ነበር፡፡ ለቡድንና ለግል የሥዕል ኤግዚቢሽን ትርኢቶችም /አንዳንዶቹን በድጋሚ/ ጀርመን፣ ዩጎዝላቭያ፣ ግሪክ፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ቼኮዝላቫኪያ፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ብራዚል፣ ስፔን፣ ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅግ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ ወዘተ… ረጅም ጉዞ የፈፀመ ሲሆን፣ በዘመናዊ አሣሣል የጥበብ ስልቱ በሀገሩ ብኩርናን ከማግኘት አልፎ ለዓለም የሥነ ጥበባት ባሕልም አንድ የግሉና ልዩ የሆነ መለዮውን ያበረከተ፣ ሀገሩንና አህጉሪቱን ጭምር ያስጠራ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር፡፡ 

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ዕድገት አርአያ በመሆኑ በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት የሀገሪቱን ከፍተኛና ዓለም አቀፋዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት በአድናቆት የተቀበለው ሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ እንደ መምህርነቱም ከ1955 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ባሉት 12 ዓመታት ውስጥ ዛሬ ለሀገሪቱ አንቱ የተሰኙ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሠዓልያን አፍርቷል፡፡ ‹‹ሞዴል አርቲስትና መምህር›› በመሆኑም በ1963 እና 1964 ዓ.ም ከወቅቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒሰቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በ1969 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ለፈፀመው ታላቅ የማስተባበር ተግባርም ከዘመቻው መምሪያ የወርቅ ሜዳልያ ተሸልሟል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ግጥም ባሕልም ውስጥ ገብረክርስቶስ ደስታ ራሱን የቻለ ሀተታ ነው፡፡ ገብረክርስቶስ በሕይወቱ ሳለ አንዳንድ ግጥሞቹ እና ቅኔዎቹ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ታትመው የወጡለት ሲሆን፣ አንዳንዶቹንም በልዩ ልዩ መድረኮች በሀገር እና በውጭ ሀገር ጭምር ራሱ አንቧቸዋል፡፡ እንደዘመናዊ ሥዕሎቹ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ የሥነግጥም ባህልም ውስጥ ገብረክርስቶስ ሀዲስ ዘር የዘራ የሀገራችን ዘመናዊ ግጥም ቆርቋሪ ነበር፡፡ ግጥሞቹ/ ቅኔዎቹ/ በሀዲስና በእንግድነታቸው ከጥቂቶቹ ተቃውሞ ቢያተርፍበትም በብዙዎቹ አድናቂዎቹ ተፈቃሪ ነበሩ፡፡

ገብረክርስቶስ ደስታ ወደ 60 ያህል የሚጠጉ ግጥምና ቅኔዎቹን ትቶልን አልፏል፡፡ ግለኛና አዳዲስ የአሰነኛኘት ዘዴ በመከተል በኢትዮጵያ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ አዲስ ንቅናቄ የፈጠሩ ግጥሞቹ እና ቅኔዎቹ የአማርኛ ቋንቋን ጣዕምና ለዛ ግልጽና ቀላል በሆነ፣ ነገር ግን ቅኔያዊ ውበትን በተጎናፀፈ የገለጻ ኃይል እስከ ባህላዊው ትውፊታችን ድረስ በመዝለቅ የኢትዮጵያውያንን ‹ነፍስ› የገለፁ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን መልክአ ምድራዊ ገጽታ ከመቅረፃቸውም በላይ፣ ለሀገሩ ባህለኛነቱንና ወገን ወዳድነቱን ባጠቃላይ- ኢትዮጵያዊ ስብእናውን አሟልተው የገለጹለት ናቸው፡፡

ከቀደምቱ የ‹‹እማ ኢትዮጵያ አርመኛ ባለቅኔዎች›› ከነዮፍታሔ ንጉሤ፣ ከእነ ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ እና ከነዮሐንስ አድማሱ ‹‹መዝሙረ ኢትዮጵያ›› ቅኔዎች በአርአያነቷ አቻ የምትሆነው የገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹ሀገሬ›› /1951 ዓ.ም/ ዛሬ ያለምንም ማዳነቅ የብዙዎቹ ፍቁረ ኢትዮጵያውያን የነፃነት ሴማ ነች፡፡ እንኳን በሕይወት ካሉት፣ በሕይወት ከተለዩን መሀል እውቁ የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁሩና ሀያሲ ሥዩም ወልዴ፣ እውቁ የሥነ-ብዕል ሊቅ ዶ/ር እሸቱ ጮሌ ወዘተ. . . ዛሬም በዐፀደ ነፍስ ሆነው/ በሕይወት ሳሉ እንደሚያደርጉት/ ‹‹ሀገሬ››ን በአርምሞ የሚያዜሟት ይመስለኛል፡፡

አብዛኛው የጥበብ ቤተሰብ በቅርብ እንደሚያውቀው በዚህች ሀገር የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ወሰጥ አንዳች አሻራ ጥሎ ያለፈው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ በተለይ ካለፈው አንድ አሠርት ዕድሜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን መድረኮች ሲወሳ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በሕይወት ያለፈው ገብረክርስቶስ ደስታ ከነበሩን ብርቅዬ የጥበብ ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ ይሁንና በዘመነ ደርግ፣ በሕይወቱ ላይ ባንዣበበ አደጋ በመስከረም ወር 1971 ዓ.ም ሀገሩን በስደት ጥሎ እንደወጣ ቀረ፡፡ ከተሰደደ ከሁለት ዓመታት እንግልት በኋላ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም. በተወለደ በ49 ዓመቱ አሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ሕይወቱ አለፈች፡፡ በወቅቱ አስከሬኑ ጭምር ‹ሀገር የከዳ› ተብሎ ለሀገሩ መሬት ሳይታደል ግብዓቱ መሬቱም እዚያው ተፈፀመ፡፡ 

ይህን የሕይወቱን ትራዤዲያዊ ፍፃሜ አስመልክቶ ዛሬ በሕይወት የሌሉትና ተቆርቋሪው የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁር ሥዩም ወልዴ ‹‹የሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ግጥሞች ››/1981ዓ.ም / በሚለው ዝክረ ጽሑፋቸው እንዲህ ደምድመውታል፡፡ 

. . . የገብረክርስቶስ ሞት ተራ የአካል ሞት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሞቱን ትራዤዲያዊ የሚያደርገው አንድ ቁም ነገር በግጥሞቹ ውስጥ እናገኛለን፡፡ . . . በተለያዩ ግጥሞቹ ውስጥ ተመልሶ እስኪረግጣት የሚናፍቃት፣ እኔም ከእናንተ ይበልጥ የምታኮራ አገር አለችኝ የሚላት፣ ሰው ከአገሩ ውጭ ሰው አይደለም ብሎ ሲተማመንባት የነበረች አገሩ፣ የሕይወቱን የመጨረሻ ሕልፈት ሳታስተናግድለት መቅረቷ ነው፡፡ እንኳን ሞቶ አስከሬኑን፣ ግድ ካልሆነበት ቀፅበታዊ ትንፋሹን እንኳን በ‹‹ባዕድ ሀገር›› መተንፈስ የማይፈልገው ገብረክርስቶስ በ1973 በኦክላሆማ ስቴት ማረፉ የሰውን ልጅ ሕይወት ወሳኝ ወቅት ጣጣ የሚያስታውስ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፡፡ …

በሕይወት ካሉትም መሀል-ዛሬ በአሜሪካ /ሜኔሶታ/ ነዋሪ የሆነው፣ ዘመነኛው እና እጅግ አድናቂ የጥበብ ባልንጀራው የ‹‹ልጅነት›› እና የ‹‹ወለሎ ወለሎታት›› ባለቅኔ ሰለሞን ደሬሣ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ሀገር ቤት መጥቶ በነበረ ጊዜ ለ ‹‹ሪፖርተር›› መጽሔት /ቅጽ2 ቁ. 13 መስከረም 1991 ዓ.ም/ ስለዚሁ ስለገብረክርስቶስ የመጨረሻ እጣ የገለፀው እንኳን የወዳጆቹን የማንኛውምንም ሰው ልብ የሚሰብር ነው፡፡ 

. . .ለኢትዮጵያውያን ፀሐፊዎችና ሠዓሊዎች ችግር ይደርስባቸዋል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ደረሰበት፤ መጨረሻው ላይ ስለ አወጣጡ የሰማሁት ነገር አለ፡፡ እሱን አላጣራሁምና አልደግመውም፡፡ ችግር ደርሶበት ወጥቶ ታሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አንድም ኢትዮጵያዊ በሌለበት ማንም በማያውቀው ሀገር ኦክላሆማ በተባለ ቦታ ሞተ፡፡ አሜሪካ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ እኔ ያለሁት ሜኔሶታ እሱ ያለው ኦክሎሆማ ነበር፡፡ ብሰማና ባውቅ ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ ሲሞት የሚያውቀው ፊት እያየ ይሞት ነበር፡፡ አሁን ሳስታውሰው በጣም ሆዴን ይበላኛል፡፡

. . . ስለ ገብረክርስቶስ ‹‹አሌፍ››አዊ በሆነው በግሌ ትውስታ መጀመር ካለብኝ፣ ገብረክርስቶስን የማውቀው በርቀት እንጂ በቅርበት አልነበረም፡፡ ይኸም ዕውቂያዬ የሚጀምረው፣ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ ከ1957 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በዚሁ ግቢ ውስጥ ስለሚገኝ፣ በዚያች ጥቁር ሬኖ መኪናው ለምጽ ህብረ መልክ ከሰጠው ገጽታው ጋር ሲከንፍ እንድ ብርቅ የምናየው ሰው ነበር፡፡ ያ ልዩ ገጽታ የነበረው የሥዕል አስተማሪ፣ በዕረፍት ሰዓት በተማሪዎቹ በፍቅር ተከቦ በተመስጦ ሲደመጥ፣ ሲያወራ፣ ሲጫወት. . . በሩቅና በየአጥሩ ጥግ የምናየው አስገራሚ ትርኢት አሁን ድረስ ይታወሰኛል፡፡ ይህ ሩቅና የአካል እውቂያ፣ ለስድስትና ለሰባት ዓመታት የዘለቀ ድግግሞሽ ሲሆን፣ ደማቁም የልጅነት ትዝታዬ ነው፡፡ 

ገብረ ክርስቶስን ያወቅሁት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነው፡፡ ‹‹መነሻ ለሥዕል›› ‹‹የሙዚቃ ድምፅ›› ‹ባለክራር›› ‹‹ከበሮ›› ወዘተ. . . የተሰኙትን ግጥሞቹን በሟቹ ወንድሜ በአድማሱ ኢሳይያስ /1946-1969 ዓ.ም/ ባለውለታነት ተዋወቅሁ፡፡ በተለይ ‹‹መነሻ ለሥዕል›› ዛሬ ውስጥ ለጨነገፈ የሠዓሊነት ዝንባሌዬ ያኔ ግን‹‹ለሮማንቲዝም››ጥበብ የጋለ ስሜቴ ቃለ መዝሙር ነበረች፡፡ 

አያልቅም ይህ ጉዞ ማስመሰል-መተርጎም 
በቀለም መዋኘት 
በመሥመር መጫወት 
ከብርሃን መጋጨት
ለማወቅ ለመፍጠር/ ባዶ ቦታ መግባት፡፡ 
መፈለግ. . .መፈለግ… 
አዲስ ነገር መፈጠር 
ከማይታየው ጋር ሄዶ መነጋገር፡፡
ሕይወትን መጠየቅ 
ሃሳብን መጠየቅ 
ዓለምን መጠየቅ
መሄድ መሄድ መሄድ 
መጓዝ ወደ ሌላ - ባዶ ቦታ መግባት
በሃሳብ መደበቅ 
መፈለግ ማስገኘት፡፡ 
አያልቅም ይህ ጉዞ. . . 

የካቲት 66 ከነጓዙ መጣ፡፡ ‹‹ዕድገት በሕብረት›› … እና በመሀል የነበረው ጊዜ ገደበን፡፡ ርቀትን በቅርበት የተካልኝ አንድ አጋጣሚ ብቻ ቢኖር፣ ለሀገሩ ስንብት የመጨረሻ የሆነውን ‹‹አጠቃላይ የሥዕል ትርኢት›› /1969/ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህል አዳራሽ ሲያሳይ ነበር፡፡ ኋላ ወቅትም አልፈቀደ . . . አጋጣሚም አላገኘንም- የእርሱም መጨረሻ በመስከረም 1971 በስደት አከተመ፡፡ ሕይወቱም በትራዤዲ የመጠናቀቁን አሳዛኝ መርዶ የሰማሁት እጅግ ሰንብቶ ነው፡፡

ቢሆንም፣ ገብረክርስቶስ በ‹‹ሞቱ ሕያው›› ሆኖ ወዲያውኑ መኖር ሲጀምር ለማየት ከበቁትም አንዱ ነኝ፡፡ ለዚሁ መንፈሱ የመጀመሪያው ወካይ አጋጣሚዬ፣ የአዲስ አበባው የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የቀለም ቅብ መምህር የነበረው ባንጀራዬ ሠዓሊ ፍፁም አድማሴ ነው፡፡ የፍፁሜ ስቱዲዮ፣ የቀድሞው የገብረክርስቶስ ደስታ ስቱዲዮ ነበረች፡፡ በየሳምንቱ አጋጣሚዬ፣ ገና ስቱዲዮው ስገባ፣ የፍፁም ምስለ ገብረክርስቶስ /‹‹ ፖርትሬት›/ ነበር የሚቀበለኝ፡፡ የሠዓሊና የቀለም ቀብ መምህር የሠዓሊ ጌቱ ሽፈራው ምስለ ገብረክርስቶስም ዓመታት /1975-1976/ ተቆጥረው የማያልቁ ውድ ወራት ነበሩ፤ ስለገብረክርስቶስ ለማውሳት ሰፊ ዕድል ሰጥተውኛል፡፡ የገብረክርስቶስ ‹‹ሞዴል›› ስብእናም፣ በፍፁሜ ሠዓሊነት፣ ገጣሚነት እና መምህርነት ወዘተ. . . ራሱን ሲገልጽም በእውን ለማየት በቅቻለሁ፡፡ / ነገር ነገር ያነሳዋል ከሆነ ይኸንኑ የገብረክርስቶስ የገጣሚነት እና የሠዓሊነት ተዋህዶ ሰብእና ‹‹ሞዴል››ነት በሠዓሊና ገጣምያኑ በእሸቱ ጥሩነህ፣ በቀለ መኮንን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ መስፍን ሀብተማርያም ክሱት ሆኖ ያየሁት ሲሆን ከዘለቁበትም ሠዓልያኑ ጀማል ካሣ፣ ጌቱ ተክሌ፣ ተስፋዬ ገብሬ፣ ሲሳይ ሽመልስ፣ ወጋየሁ አየለ፣ አገኘሁ አዳነ ወዘተ. . . የዚሁ ‹‹ተፅዕኖ›› ባለቤት ናቸው፡፡ 

እና የፍፁሜ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ጀርመን ጉዞ ስለገብረክርስቶስ ሌላ ውድ አጋጣሚ ተክቶልኛል፡፡ ገብሬ ለመጨረሻ ጊዜ ለሦስት ዓመታት የሠራበት /1969-1971/ እና ምናልባትም እንደመጀመሪያው ብሔራዊ ጋለፊ ሊቆጠር የሚችለው የአዲስ አበባው ማዘጋጃ ቤት የባህል አዳራሽ ስቱዲዮ ቤተኛ የመሆን ዕድል አጋጠመኝ፡፡ ሠዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀበተማርያም፣ የስቱዲዮው ተረካቢ ብቻ ሳይሆን፣ የገብረክርስቶስ ደስታ የመፈስ ሀብታት ጎተራ መሆኑ የላቀ ዕድሌ ሆነ፡፡ በተጨማሪ የባህል አዳራሹ ዕውቅ ተዋንያን ሥዩም ተፈራ፣ ሱራፌል ጋሻው፣ አልአዛር ሳሙኤል ወዘተ… የገብረክርስቶስ ረሀብ ጥማቴ-ምሉዕ ሕብስትና ጽዋ ሆኑ፡፡ ኋላ ጋሽ ስብሐት፣ ባሴ ሀብቴ፣ ደምሴ ጽጌ፣ ነቢይ መኮንን፣… ገብረክርስቶስ እንደጠቢብ ርዕሰ ነገሬ እንዲሆን የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በኋላም የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁሩ የሥዩም ወልዴ፣ የተማሪዎቹና የዛሬዎቹ አንጋፋ ሠዓልያን የእነ እሸቱ ጥሩነህ፣ የነ ታደሰ መስፍን ወዘተ… ዕውቂያ የበለፀገ ነገር አስገኝቶልኛል፡፡ ይህ ሁሉ ተባብሮ ከርቀት - ወይ ቤተሰብ ቤተኛነት ብሎም የትውስታው ዘካሪ ከመሆንም እንደ እድል ወደ ሕይወት ታሪኩ ምርመራና ጥናት አድርሶኛል፡፡ 

ገብረክርስቶስ ደስታ የቤተክህነት ሊቅ ከሆኑት፣ ከአለቃ ደስታ ነገዎ /1849-1947/ እና ከወ/ሮ ፀጸደማርያም ወንድማገኘሁ ጥቅምት 5 ቀን 1924 ዓ.ም በሐረር ከተማ ተወለደ፡፡ ለወላጆቹ በስተርጅና የተገኘ የመጨረሻና 10ኛ ልጅ ነበር፡፡ እናቱ የሞቱት ገና የመንፈቅ ልጅ ሳለ ነው፡፡

የገብረክርስቶስ የጨቅላነት ጊዜ የተተካው በልጅነት እድሜ አበሳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የሦስት ዓመት ሕፃን ሳለ ነበር … ፋሺስት ኢጣሊያ በሐረር በወልወል ግጭት ሰበብ የመጀመሪያውን ወረራ የፈጸመ፡፡ በዚህም የልጅነት ዕድሜውን በስደት ጀመረው፡፡ በ1927 ከሐረር አዲስ አበባ፡፡ ሕፃኑ ገብረክርስቶስ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አዲስ አበባና ሕዝቧ በፋሽስት ሲፈጁ እዚሁ ነበር፡፡ ከልጅነት መሪር ትዝታዎቹ አንደ እናት ሆነው ካሳደጉት አባቱ መለያየቱ፣ የአባቱ በጣሊያኖች መታሠርና መጋዝ፣ ከእሥራታቸው ሲፈቱ ወደ ሐረር መመለሱ፣ ፋሺስቶቹም የሀገሬውን ልጅ ለዓላማቸው መኮተኮቻ እንዲሆን በከፈቱት ‹‹ቢላላ›› ትምህርት ቤት ከአባቱ ጉያ ተነጥቆ እንዲገባ መገደዱ ወዘተ… ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ኋላ በጉልምስና እድሜው ላይ ይጻፈው እንጂ ‹‹የደም ቀን›› /1959/ የሚለው የፀረ ፋሺስት ትውስታ ግጥሙ በቀጥታ ለየካቲት 12ቱ ሰማዕታትና ለልጅነት መራር ተዝብቱ ማካተቻ ነው፡፡ 

የገብረክርስቶስ ልጅነት- መራርም ሆነ ደማቅ ትውስታ የተተካው፣ ከነፃነት በኋላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረሩ የራስ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቆ /1933-1938/ ለቀጣይ ትምህርቱ አዲስ አበባ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ያለው ነው፡፡ መቼ እንደጻፋት አትታወቅ እንጂ፣ ‹‹ትዝታ›› የምትለው ግጥሙ፣ ይህንኑ የልጅነት ሕይወት ትዝብቶቹን የከተበችና ምናልባትም የጉልምስና ዘመኑ ስብእና መቅድማዊ መዝገቡ መሆኗን አለጥርጣሬ መቀበል ይቻላል፡፡ 

እና ይህች ቀዳሚቱ ክት ልጅነቱ፣ ጉልህና ደማቅ ሆኖ ለተገለጠ ለኋላ የጉልምስና ስብእናው ዓይነተኛዋ ምንጭ ሳትሆን አልቀረችም፡፡ እንደእኔ አመኔታ፣ ሦስቱ የሰብእናው ሕቱም ባሕርያት- የገብረክርስቶስ ሠዓሊነት፣ የገብረክርስቶስ ገጣሚና ባለቅኔነት እና የገብረክርስቶስ ብሔረተኛነት - ከዚሁ ከልጅነት ማደጎው ጥልቅ ሚስጢር የተቀዱ ናቸው፡፡ ሥዕል ‹እናቱ›፣ ግጥምና ቅኔ ‹‹አባቱ› የሆኑት ገብረክርስቶስ፣ በሁለቱ ተዋህዶ ገናን ብሔረተኛ የመሆኑ ምሥጢር ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡

አንድም፣ የገብርክርስቶስን ክት የልጅነት ሕይወት፣ በሕይወቱ ‹ታላቅ ሰው› አድርጎ ከሚቆጥራቸው አባቱ ጋር አቆራኝቶ ማየትም ይቻላል፡፡ የሥዕልና የቅኔ ፍላጎቱን ከመኮትኮትና ከማዳበር ሌላ፣ የልጅነት አቅሙ በሚፈቅደውም መጠን፣ ስለ ሀገራችን ሊቃውንት፣ የጥበብ ሰዎችና የታሪክ ሰዎች ይተርኩለት እንደነበር ቤተሰቡ ይናገራል፡፡ ከአባቱ ጋር አደባባይ በሚወጣበትም ጊዜ ከየአዛውንቱ ጋር ያደርጉት የነበረውን ቁም ነገራም ውይይት ሁሉ፣ ልቦናውን ሰጥቶና ጆሮውን አቅንቶም ያዳምጥ ነበር፡፡ ጥቃት የማይወዱት፣ እጅግ ርህሩህና ቅን የነበሩት አባቱ፣ ለተቸገረ የሚያደርጉትን ብፅአት ገብረክርስቶስ ያስተውል ነበር፡፡ ኋላ ለተቸገረ አዛኝ፣ ድሃ-ወዳድ፣ ቸርና ለጋስ የነበረውን ገብረክርስቶስን ይህንን እና ይህን የመሳሰለው ሁሉ ገና በልጅነቱ -አንደበቱን በጥዑም ቃለ መዝሙር፣ ግጥምና ቅኔ፣ ልቦናውንና እጁን በቀለም በሥዕል ህሊናውንም በሀገር ታሪክና በዕውቀት ብሎም ጥልቅ በሆነ የወገን ፍቅር-የከተበው ይኸው ከአባቱ ጋር የነበረው ቅርብና ምሥላዊ ቁርኝት ነው፡፡ 

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በገብረክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ብርቱ ተፅዕኖ ያላቸው እኚህ አባቱ በ1947 ዓ.ም መስከረም 21 ያረፉ ሲሆን፣ የጥልቅ ቅኔዎቹ ቁንጮ ሊሆን በሚችለው ‹እረፍት አርግ አሁን› /1958/ በሚለው የግጥም ዝክሩ፣ ስብእናቸውን በጉልህ ቀርፆልናል፡፡ ትውስታውን ለእርሳቸው ያስፍረው እንጂ ዛሬ ‹መታሰቢያነቱ› ጭምር በኢትዮጵያ ሥነ ጥበባት መድረክ ላይ ‹የሕይወት ሩጫውን› ለጨረሰ ለራሱ ለገብረክርስቶስም እንደትንቢት ሆኖ እንደገዛ ራስ ኑዛዜው ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡ ‹እረፍት አርግ አሁን› . . . ለራሱ ለገብረክርስቶስ ሊባል ይችላል፡፡

ክፍል ሁለት

ገብረክርስቶስ መሳል የጀመረው ገና በሕፃንነቱ -ዕውቅ ከነበሩት ቁም ጸሐፊ ፣መጻሕፍት ደጓሽና ባህላዊ የሃይማኖት ሠዓሊ አባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ጉያ ሥር ሆኖ ነው፡፡ ባገኘው ነገር ቅርፃ ቅርፅ መሥራት ይወድ የነበረው ገብረክርስቶስ ለሥዕል ለነበረው አድልዎ - የልጅነት ቀልቡ እየገፋፋው- መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ሥዕሎች በፈጠራ ይሠራ እንደነበር ቤተሰቡም ሆነ የትምህርት ቤት ባልንጀሮቹ ዛሬ ድረስ በትዝታ ያነሱታል፡፡ ለዚህም በክብር ተቀምጣለት፣ ለጉልምስና ዘመኑ ትዝታ ከበቁለት ሥራዎቹ መሀል አንዲቱ የሰባት ዓመት ሥዕሉ ‹‹ምስለ ፍቁር ወልዳ›› ምስክር ናት፡፡ 

ከሌላ በኩል፣ አብረውት ከተማሩት መሀል፣ ሐረር ተወልደው ያደጉትና ዛሬ በኢትዮጵያ የአማርኛ ዘመናዊ ግጥም ስልት -ልዩ የአሰነኛኘት ዘዬ ያላቸው አቶ ሰይፉ መታፈሪያ አንዱ ናቸው፡፡ ገብረክርስቶስ ደስታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ከሐረር አዲስ አበባ እስከሄደ ድረስ፣ ስለሱ የሚያስታውሱት አላቸው፡፡ 

ገብረክርስቶስ! ያኔ በክፍል ደረጃ ይበልጠኝ ነበር፡፡ በጣም የሚሮጥ ቀልጣፋና ሳይደክም የሚጫወት ነበር፡፡ ቴኒስም እንጫወት ነበር፡፡ አቋሙ ሁሉ የስፖርተኛ ነበር፡፡ . . . ሌላ ትዝ የሚለኝ! ያኔ በባዶ እግር ነበርን፡፡ ምንለብሰውም ቁምጣ ነበር፡፡ ታዲያ ማስታወስው ጧት ወይ በእረፍት ሰዓት ቁጭ ብለን ፀሐይ ስንሞቅ፣ ቁጭ ብሎ ጉልበቱ ላይ ይሥል የነበረው ነው፡፡ በሚሥላቸው እደነቅ ነበር፡፡ ያለምንም ጥርጥር የስን-ክን ሰው ነበር፡፡ በስን-ክን ስሜት የተነደፈ ልጅ ነበር፡፡ . . . ዛሬ ግን የሚያሳዝነው አፅሙን እንኳ ለሀገሩ መሬት ማብቃት አለመቻላችን ነው፡፡ 

ገብረክርስቶስ ደስታ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ የመጣው በ1939 ነው፡፡ በያኔ የኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት /የዛሬው መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ/ ተመደበ፡፡ ከሐረሩ የጢቆ አደሬ መካነ ሥላሴ ደብር አለቃ ከነበሩት ከአለቃ ለማ ኃይሉ ልጅ- ከመንግሥቱ ለማ ጋር በወግ ለመተዋወቅ የቻሉትም እዚሁ ነበር፡፡ ገብሬ ፣ትምህርቱን በአዳሪነት ጀመረ፡፡ 

ከዚሁ ከኮተቤ ቆይታው ሊዘከር የሚችል ነገር ቢኖር አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ መምህሩ ጋር ተጋጭቶ ከትምህርት ቤት መታገዱ ነው፡፡ እግዱም በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ነዋሪ የነበረው የዚህ መምህሩ ውሻ ሊነክሰው ሲጋበዝ ውሻውን በመደብደቡ ነበር፡፡ መምህሩ ለውሻው መመታት ተቆርቁሮ - ዳይሬክተሩ ላይ ይከሰዋል፡፡ ዳይሬክተሩም አስጠርቶት ‹‹ይቅርታ ጠይቅ! ››ይለዋል፡፡ ‹‹እኔ ይቅርታ ልጠየቅ ሲገባ፣ ይህ አግባብ አይደለም›› ይላል፡፡ ለሱ መታዘኑ ቀርቶ! ‹ለፈረንጅ ውሻ› ሲዳላ በማስተዋሉ፣ በደመ-መራራነት ተናገረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከበላዮቹ ጋር በመሟገቱ እንደ ‹ድፍረት› ተቆጥሮበት እንዲያውም እስከመታሠር አደረሰው፡፡ ለግሳፄ ተብሎ በያኔው የሦስተኛ ሻለቃ ክቡር ዘበኛ ካምፕ ለአራት ወራት ያህል ታሠረ፡፡ 

ያኔ በልጅነቱ-በጣሊያን ወረራ -የ‹‹ባዕድ ሀገር›› ጥቃትን ያየው ገብረክርስቶስ፣ ‹‹የፈረንጅ ዕውቀቱን እንጂ ክፋቱን የማይፈልገው›› ገብሬ፣ በበሰለ መንፈስ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹የባዕድ ሰው›› ጥቃትን እስከ እስር ድረስ ተጋፈጠ፡፡ በዚህ ሁኔታ ትምህርቱን ለማቋረጥ ቢገደድም፣ ይህ ጊዜ እንደዝንባሌው የመሣል፣ አንድም በጥበቡ ዘርፍ ጭምር በስፋትና በጥልቀት በማንበብ መልካም አጋጣሚን ያተረፈለት ነበር፡፡ ከአእምሮው ብልጽግና ሌላ፣ ገብረክርስቶስ ከእግር ኳስ ችሎታው በተጨማሪ አካሉን ለማዳበር የአካል ማሠልጠኛ ጂምናስቲክ ማዘውተርና ሰውነቱን በስፖርት መገንባት የጀመረው ይኼኔ ነበር፡፡ 

ያቋረጠውን ትምህርት፣ በለጣቂው ዓመት የጀመረው፣ ያኔ ጉለሌ አዲስ በተከፈተው የጄኔራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ዊንጌት መግባቱ፣ ከቀለም ትምህርቱ ጎን ስለጥንታዊውና ዘመናዊው የአውሮፓ ሥነ-ጽሑፍና ሥነ ጥበብ በሰፊው ለማንበብ ሌላ ልዩ አጋጣሚን ፈጥሮለታል፡፡ የገብረክርስቶስ ወርቃማ የወጣትነት ወቅት፣ ይህ ዊንጌት ያሳለፈው የሦስት ዓመታት ጊዜ ነበር፡፡ የቀለም ትምህርቱ፣ የግል ንበባቡ፣ ስፖርቱ ወዘተ፡፡ በቀለም ትምህርት ትጋቱም ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ተሸላሚ ለመሆን ችሏል፡፡ አድናቂውና የጥበብ ባልንጀራው ከነበረው ከሰሎሞን ደሬሣም ጋር የተዋወቀው በዚሁ በዊንጌት የተማሪነት ወቅት ነበር፡፡ 

ከዊንጌት ደማቅ ትዝታዎቹም የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ገብረክርስቶስ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለ፣ የትምህርት ቤቱ ዓመታዊ በዓል ሲከበር፣ የተማሪዎች የሥዕል ኤግዚቢሽን ቀርቦ ነበር፡፡ በበዓሉም ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተገኝተው ነበር፡፡ ታዲያ ያኔ በኤግዚቢሽኑ -ለሀገሪቱ የሥዕል ባህል አዳዲስና እንግዳ የሆኑ የአሣሣል ስልቶችን ይዞ የቀረበው ገብረክርስቶስ ነበር፡፡ የልጅነት ማደጎውንም የምታስታውሰው ‹‹የሐረር ገበያ›› ሥዕሉንም ያቀረበው በዚህ ኤግዚብሽኑ ነው፡፡ እና ‹‹ሪአሊስቲክ›› ‹‹ሰሚ አብስትራክት›› እና ‹‹ አብስትራክት›› /ረቂቅ ወይም ምስጢራዊ/ የሆኑ ዘመናዊ ሥዕሎች ነበሩ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ታዲያ ንጉሡ በአድናቆት ጭምር አነጋግረውት ነበር ይባላል፡፡ እኒያን ‹‹አብስትራክት›› ሥዕሎቹን እያዩለትም ‹‹. . .መቼም ነገሩን አጥተኸው ሳይሆን - ሆነ ብለህ ለማበላሸት ብለህ ነው እንዳሉት ››ይነገራል-ፈገግታ በተቀላቀለው አንደበት፡፡ 

ገብረክርስቶስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከዊንጌት በ1942 አጠናቀቀ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳለ ነበረ በለጣቂው ዓመት በ1943 ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተከፈተው፡፡ የኮሌጅ ትምህርት ለመቀጠል ከገቡት ከመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መሀል አንዱ ገብሬ ነበር፡፡ ፍላጎቱ ሥነጥበብ ለማጥናት ነበረ፡፡ ይሁንና ሀገሪቱ ይህን ፍላጎቱን ልታሟላለት አልቻለችም፡፡ የገሀሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና በመሆኑ ፣ከዚሁ የሀገሪቱ የወደፊት ግስጋሴና ዘመናዊ ዕድገት አንፃር ራሱንና ሀገሩን ለመርዳት፣ ገብሬ እርሻ ማጥናት እንዳለበት ወሰነ፡፡ በሳይንስ ፋካልቲ የሥነ-ሕይወት / ባዮሎጂ/ ዲፓርትመንት ተማሪ ሆኖ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ይህ የኮሌጅ የመጀመሪያ ዓመት ለገብረክርስቶስ መልካሙ ጊዜ ነበር፡፡ በአዲስ የትምህርት ሥርዓት፣ በአዲስ ፍላጎት ከመማር ሌላ፣ በስፖርቱም በኩል ለፋኩልቲው የእግር ኳስ ቡድን ምርጥ ተጫዋች ነበር፡፡ ሆኖም ሁለተኛ ዓመት ካጋመሰ በኋላ፣ የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ ወጣ፡፡ 

ከኮሌጅ ሕይወት ‹‹ስደቱ›› በኋላ፣ ለጣቂዎቹ አምስት ዓመታት /1944-1948/ ለገብረክርስቶስ አታካችና መራራ ወቅቶች ነበሩ፡፡ ገብረክርስቶስ ‹ራሱን ፍለጋ› ያልገባ ያልወጣበት ያልወረደውና ያልጣረው ነገር አልነበረም፡፡

ኮሌጁን አቋርጦ መጀመሪያ ሥራ የያዘው በአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ነበር፡፡ የአፈር ምርመራ ባለሙያ ሆኖ በዚህ ድርጅት ጥቂት ጊዜያት ሠራ፡፡ በሥራው የመንፈስ እርካታ ባለማግኘቱ ጥሎት ወጣ ::በመሆኑም ትንሽ ጊዜ እቤት ማሳለፍ ተገደደ፡፡ ቆይቶ ግን - ተወልዶ ባደገበት ሐረር ሥራ አገኘ፡፡ ሲንክላር የተሰኘው የአሜሪካ ነዳጅ ፈላጊ ድርጅት ቀጥሮት ኦጋዴን ወረደ፡፡ በጤና ምክንያት ዓመት እንኳ ሳይቆይ ሥራውን ጥሎ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ አሁንም ትንሽ ጊዜ ቤት ማሳለፍ ግድ ሆኖበት ነበር፡፡ በሥዕል ዝንባሌው ምሉዕ መግለጫ ጊዜ ያገኘበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ 

ቆይቶ ግን በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ ተቋማት ከሚባሉት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደስታስቲሺያን የሠራ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ለተወሰነ ጊዜ ሠርቷል፡፡ ዛሬ በባንክ ባለሙያዎች ክበብ እና በሞርጌጅ ባንክ የሚገኙ ሥዕሎቹ ከዚሁ ቆይታው ጋር የሚዛመዱ መታሰቢያዎቹ ሳይሆኑ አልቀረም፡፡ ይሁንና እዚያም ብዙ አልቆየም፡፡ ይሻላል በሚል እምነት፣ በስብስቴ ነጋሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጠረ፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ጂኦግራፊ እና ጠቅላላ ሳይንስ አስተማረ፡፡ በዚህም አልገፋበትም፡፡ 

በመጨረሻ ‹‹ራሱን ፍለጋ›› ላይ የነበረው ገብረክርስቶስ ‹‹ሥራ›› የሚባል ነገር እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ቤቱ ሆኖ-በሥዕል ሥራው ላይ ብቻ በመጠመድ ያለዕረፍት መሥራት ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር- በሕይወቱም በዝንባሌውም የመጀመሪያ እርካታ ያገኘበትን ፍሬ የቀመሰው፡፡ በ1946 በኢትዮጵያ የሥነጥበብ መድረክ፣ እንደ ጥበብ ወፍ ብቅ አለ፡፡ በወቅቱ የአሜሪካ የማስታወቂያ ድርጅት አካል በነበረው ቤተ መጻሕፍት ዘመናዊ የአሣሣል ስልቶቹን ያስተዋወቁ እና የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የዳሰሱ የ‹‹ድሆች ቤተሰብ›› ምዕመናን ›› ወዘተ. የተሰኙ ስዕሎቹን ትርኢት አሳየ፡፡

በጀርመን ከሄደ በኋላ በቦን፣ ከተለያዩ የጀርመን፣ የፈረንሳይ እና የሩሲያ አርቲስቶቸ ጋር በቡድን ሆኖ በጀርመን የሥነጥበብ አፍቃሪዎች ዘንድ ዝና ያተረፈለትን የሥዕል ትርኢቱን በቤትሆቨን የአርት አዳራሽ ለማሳየት በቃ፡፡ ለልዩ ተሰጥኦው የጀርመን መንግሥት የአንድ ዓመት ነፃ የመኖሪያ ፍቃድና ስቱዲዮ ስለሰጠው ገብረክርስቶስ የአውሮፓን ዘመናዊ የጥበብ መንፈስ እና የአሠራር ስልት እያጠና ለተጨማሪ አንድ ዓመት ቆየ፡፡ በወቅቱ በአውሮፓ የ‹‹ኤክስፕሪሽኒዝም›› የሥነ ጥበብ ፈለግ ተከታይ አርቲሰቶች ጋርም አብሮ የመሥራት አጋጣሚን አደለው፡፡

በዚሁ የጀርመን ቆይታው ከሚያፈቅራት ሀገሩ፣ ከሚወደው ቤተሰቡና ትዝ ከምትለው የትውልድ መንደሩ ርቆ በ‹ባዕድ ሀገር ››የናፍቆት ደም ያረገዘ ብዕሩን መስበቁ አልቀረም፡፡ ‹‹‹ሀገሬ ››እና ‹‹እንደገና›› የተሰኙ ፍቁረ ኢትዮጵያ ውብ ቅኔዎቹ የተማጡት ያኔ ነበር፡፡

ምናልባትም ናፍቆቱን እና አንዳንድ የመንፈስ ችግሩን በጋራ ይካፈሉት ከነበሩት እና በጀርመን ሀገር በተለያዩ ከተሞች ይማሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከነዕጓለ ገብረ ዮሐንስ /ዶ/ር/፣ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ /ዶ.ር/፣ አምሳሉ አክሊሉ /ዶ.ር/፣ አሉላ አባተ /ዶ.ር/፣ ኃይለገብርኤል ዳኜ /ዶ.ር/፣ ወዘተ ጋር መተዋወቅ የቻለው በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ 

ገብረክርስቶስ ካንድ ዓመት ልፋት፣ ጥረትና ድካሙ ጋር ባጠቃላይ ጀርመን ሳለ 90 ያህል ድንቅ የተባሉ ሥዕሎቹን ሳለ፡፡ ስብእናን የሚገልጸውን ‹‹እኔ በገዛ እጄ›› የተሰኘ የገዛ ገፀ ምስሉን የሣለው በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ ባህላዊውን የሀገራችንን እና ዘመናዊውን የአውሮፓ ጥበብ እና የሥልጣኔ መንፈስ በገዛ መንፈሱ የዕውቀትና የጥበብ ድልድይነት አዋህዶ በዘመናዊነት ኢትዮጵያ ሀዲስ የጥበባት ዘር ሊዘራ፣ ሞገደኛ የጥበብ ተምኔቱን የፀነሰው ይኼኔ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የገናና ስብእናው ዘመናዊና ህብራዊ ትርኢቶች በውል መገለጽ የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 

ታዲያ የጀርመን ቆይታ ሥዕሎቹ በጀርመን ሃያስያን እንደተገለጹት የአርቲስቱን ዘመናዊ ጠቢብነት የሚያውጁለት፣ የጀርመንን መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንድም የአካላዊ ሥልጣኔዋን ማቴሪያላዊ የኢንዱስትሪ ውጤት ቁሳቁስ እንዲሁም መልክአ ሰብእ የሚገልፁ ብሎም ከገዛ ሀገሩ ሕይወት እና ትዝታ ከገዛ ስብእናው ጭምር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አሣሣል ቴክኒካቸውም ግማሽ ምሥጢራዊነትን እና ምሥጢራዊነትን /ሰሚ አብስትራክትና አብስትራክት/ እንዲሁም እውነታን /ሪአሊስቲክ/ የሚያንፀባርቁ ነበሩ፡፡ እነዚህን ጠቅላላ ሥራዎቹን በዚሁ በ1954 ኮሎኝ ከተማ በሚገኘው በኩፐርስ ጋለሪ አዳራሽ፣ የያኔው የኢትዮጵያዊ አምባሳደር /ሜ.ጀኔራል ከበደ ገብሬ/ በተገኙበት ለጀርመን አፍቃሬ ጥበባት አሳየ፡፡ ትርኢቱ አድናቆት ከማትረፉም በላይ፣ ገብረክርስቶስን በጀርመን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና የመጀመሪያው ድንቅ አፍሪካዊ ሠዓሊ የሚል ማዕረግ አስገኝቶለታል፡፡ ይኸው ክብር እና ዝና ከጀርመን ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ዘንድ ሞገስ አስገኝቶለት በስታድትሆል አዳራሽና በጉድስበርግ የ90 ሥዕሎቹን ትርኢት የማሳየት ተጨማሪ ክብር አገኘ፡፡ 

ገብረክርስቶስ ወደ ሀገሩ ከመመለሱ በፊት አውሮፓን እንደጠቢብም እንደ ‹‹ቱሪስት››ም ዞረ፡፡ ጥንታዊቱን የፍልስፍና እና የጥበብ አምባ ግሪክን፣ ቤልጅግን፣ ፈረንሳይን፣ ስፔንን እና ጣሊያንን ጎብኝቶ እና የሥዕል ኤግዚቢሽኖቹን አሳይቶ በመጋቢት ወር 1954 ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ 

የሀገሩን ወጣቶች የሥዕል ጥበብ ለማስተማር ብርቱ ተምኔት እንዳለው የገለጸው ገብረክርስቶስ በ1955 ያኔ በትምህርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር ሥር ይገኝ በነበረው በአዲስ አበባው ብቸኛ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሥራውን ጀመረ፡፡ ራሱን በማስተማር ሙያ ላይ አሰማርቶ፣ ሙሉ ጊዜውንም ለጥበብ ሰጥቶ ያለዕረፍትና ድካም በመሥራት ከጀርመን ሀገር በተመለሰ በዓመቱ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተገኙበት በአ.አ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ግንቦት 3 ቀን 1955 ዓ.ም የ72 ሥዕሎቹን ኤግዚቢሽን አሳየ፡፡ 

እኒሁ ሥዕሎቹ ባመዛኙ በወቅቱ ጀርመን ውስጥ በዘመናዊ ጥበብ ስልት ረገድ ገናና የነበረውን ‹‹ኤክስፕሬሽኒዝም›› የተሰኘውን የሣሣል አቅጣጫ የተከተሉ፣ በይዘታቸውም የመልክአምድር፣ የቁሳቁስና የመልክአ ሰብእና የያዙ ድርሰቶች ሲሆኑ በቴክኒካቸውም የውሃ ቀለም፣ የዘይት ቀለም ቅብ እና የግራፊክስ ሕትመት ሥራዎች ነበሩ፡፡ እኒሁ ሥራዎቹ የጠቢቡን ልዩ ክሂሎትና አዲስ የሥነጥበብ አቅጣጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ያበሰሩ እና የተለሙ ነበሩ፡፡ 

ሁነቱ አድናቆትና ተጋጭ የሆኑ አስተያየቶችን አስከትሎበታል፡፡ ከልማዳዊው ሥዕል ስልት ፍፁም አፈንግጠው ለቀረቡት ሥዕሎቹ ለ‹‹ሀገሪቱ ባዕድ ናቸው ››የ‹‹ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናዊ አርት አይገባውም ›› ‹‹ጊዜውን የተከተሉ አይደሉም ›› የሚሉ የወቀሳ አስተያየቶች ጎርፈው ነበር፡፡ እውቁ የበረከተ መርገም›› ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ/ገሞራው/ እንኳ ‹‹መዳልወ ኪነት›› በሚለው ግጥሙ የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል ‹‹እውነት አብስትራክት አይደለችም ››በሚል ብሂል፡፡ 

ገብሬ ለእኒህ ‹‹ወቀሳዎች ››በእርጋታና በአስተውሎት ሊመልስ ሞክሯል፡፡ ይህም ግንቦት 5 ቀን 1955 ታትሞ በወጣው የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ላይ በወግ ተዘግቦ እናገኘዋለን፡፡ 

‹… የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ /1946/ ለመጀመሪያ ጊዜ ላሳዩት የአብስትራክት አርት ሥዕሎቼ ብዙ ደጋፊዎች አግኝቼ እንደነበር አስታውሳሁ፡፡. . ./የአሁኖቹ/ ሥዕሎቼ በአዲስ አቅድ የተዘጋጁ ቢሆኑም፣ ለሀገራቸው ሕዝቦች /ለአውሮፓውያን/ እንግዳ ጥበቦች አይደሉም፡፡ . . . የኢትዮጵያም ሕዝብ ይህን በመሰለው የፈጠራ አሠራር፣ ያላያቸው ልዩ ልዩ መልክ ይዘው በጣና ባሕር ባሉት አብያተ ክርስቲያናትና በደብረ ዳሞ እንዲሁም በላሊበላ ሕንፃዎች በቅርፅ ተሰርተው ይገኛሉ፡፡› 

ሲል ገልፆአል፡፡ ገትጋታ ባህለኞችም በአሽሙርና በማካኪያስ አላዋቂነታቸውን ደጋግመው ሲያስተጋቡም በወቅቱ በእርጋታና በአስተውሎት ሳይሰለች ምላሽ ሊሰጥ ሞክሯል፡፡ 

‹‹… እኛ በመልማት ላይ በሚገኙት ሀገሮቻችን ዘመናዊ ሕንፃዎችን፣ ዘመናዊ አውቶሞቢሎችን፣ እናሽከረክራለን፡፡ በጠቅላላ በቴክኖሎጂ፣፣ በሳይንስ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ኢንተርናሽናል / ዓለማቀፋዊ/ ሥራዎችን እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ኪነጥበብ ብቻ ለምን ይለያል?... ሁሉም የነበረውንና ያለውን ጠብቆ ለማቆየት ብቻ መሰለፍ የለበትም፡፡ እንደሌላው ዘርፍ ሁሉ ለኪነጥበብም መሥራትና አስተዋዋቂም ይፈልጋል፡፡…..››

አለ ገብረክርስቶስ፡፡ ባጠቃላይ አዲሱንና ዘመናዊውን የጥበብ መንፈስ ከአውሮፓይቱ ጀርመን ተክኖ እና በ‹‹ፋውስታዊ ››ተምኔት የመጣው ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ለሁለቱ የኢትዮጵያ /ባሕላዊ/ እና የአውሮፓ /ዘመናዊ/ ሥልጣኔ ጥበባት አማካይ ጠቢብ ሆኖ በገዛ ወዙ የተጥለቀለቀ አዲስ የመንፈስ ሕይወት ራዕዩን በቀለምና በቡሩሹ ኃይልና ውበት አዲስ ዓለም ለዚህ ኢትዮጵያ ትውልድ ገለጠ፡፡ እና ‹‹ረቂቅ›› ‹‹ሥውር›› ‹‹ምስጢራዊ›› ‹‹ግልጽ ያልሆኑ›› ‹‹አብስትራክት›› ወዘተ. የሚል ‹‹ክርስትና ስም›› ያተረፉቱ ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ የሥዕልና የሥነጥበብ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ሀዲስ ምዕራፍ ከፈቱ፡፡ ‹‹መልስ ወዳገር ቤት፣›› ፣‹‹የካቲት 12››፣ ‹‹ያለፈው መልካሙ ጊዜ››፣‹‹የሐረር ገበያ››፣ ‹‹እኔ ነኝ››፣ ‹እኔ በገዛ እጄ›፣ ‹‹ጎልጎታ›› ‹‹ጂፕሲ ልጃገረድ››፣ ‹‹ቀይብርሃን››፣ ‹‹የድሆች ቤተሰብ››፣ ‹‹በራሪ ወፍ››፣ ‹‹በቁኤት››፣ ‹‹ ጠላቂ ጀምበር››፣ ‹‹ፀደይ›› ዘተ. የተሰኙት ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል ታሪክ አንዳች የሀዲስ ፍኖት ፋና ወጊ ሆነው ሀዲስ የሥነጥበብ ምዕራፍ ገብረክርስቶስ መክፈቱን በእርግጠኝነት አውጀውለታል፡፡ 

ገብረክርስቶስ ደስታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ የጥበብ ሐተታ አይደለም ፡፡ ባጭሩ፣ ነቢይ በ‹‹ሀገሩ አይከበርም›› እንዲሉ ወይም ‹‹ትንቢት ይቀድሞ ለነገር ››እንዲሉ የሕይወት ትራዤዲው ትንቢት ነው መሰል ከሀገር ተሰዶ ከመውጣቱ ትንሽ ቀደም ብሎ በ1969 በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከልጅነት እስከ ጉልምስና ድረስ ያፈራቸው የምርጥ ሥዕሎቹን ኤግዚቢሽን ‹‹አጠቃላይ የሥዕል ትርኢት›› በሚል ለመጨረሻ ጊዜ አሳይቶ ለመጨረሻው አልፏል፡፡ 

መጋቢት 21 ቀን 1973 በ‹‹ባዕድ ሀገር›› በሞት የተለየን እና የዚህ ትውልድ ‹‹የከርታታ ነፍስ ምሳሌ›› የሆነው ገብረክርስቶስ ያ ታላቅ ኢትዮጵያዊ እና ዓለም አቀፋዊ አርቲስት ከተለየን እነሆ ሃያ ዓመታት ሊመጡ ነው፡፡ 

ይሁንና ዛሬ በጥበብ ሥራዎቹ መታሰቢያነት መሀላችን ሕያው ነው፡፡ ይህንኑ ተአምኖዬን የሚያፀድቅልኝና በእያንዳንዱ አፍቃሬ ጥበብ ዘንድ ዛሬም ሕያው መሆኑን የሚመሰክር ማራኪ ዝክር ሳልጠቅስ ማለፍ አይሆንልኝም፡፡ በቅርቡ፣ የገብረክርስቶስ ዘመነኛ እውቁ ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም በቅርቡ ባወጡት ‹‹ሹክታ›› በተሰኘ የትውስታ መድብል /1992/ ውስጥ ገብረክርስቶስን እና መሰል ጠቢባንን ‹‹የእግዜር ባውዛ›› ሲሉ ሰይመዋል፡፡ ለዚህ ትውልድ ገብረክርስቶስ ከዚህ በላይ ምን ድንቅ ዝክር ይኖራል?!! 

ሪፖርተር መጽሔት፤ጥቅምት 1993 ዓ.ም

ብርሃነ መስቀል ደጀኔ

No comments: