April 27, 2010

ዴዚዴራታ/መሰረታዊ የኑሮ መመሪያ


ምድር ብለን በምንጠራው ፕላኔት ውስጥ ካሉ ፍጥረቶች ሁሉ፤
 አንተ የላቅክና እጅግ የመጨረሻው ጠቃሚ ፍጥረት ነህ።
ነገሩ ለጊዜው ግልጽ ሆኖ ባይታይህም የተፈጠርክበት አንዳች ምክንያት አለ፤ 
ባይኖርማ ኖሮ እንደ ብዙ ያልተወለዱ ፅንሶች ጭንጋፍ ሆነህ በቀረህ ነበር።
የሰው ልጅ የከበረ ሀብቱ ትጋቱ ነውና፤ 
የተፈጠርክበትን ምክንያት ፈልጎ በማግኜት ላይ ትጋ!
አንተ ልዩና ድንቅ ፍጡር በመሆንህ በራስህ ልትደሰት፤ 
ተገቢውን ክብርና ዋጋም ልትሰጥ ይገባሃል። 
ማፍቀርም ሆነ መፈቀር የምትችለው ለራስህ ተገቢ የሆነ ፍቅር ሲኖርህ ብቻ ስለሆነ፤
 ራስህን ከነድክመትህም ቢሆን ተቀበለው።
 ፍቅር ለጨለማ መንገድ ብርሀን፤ ለነፍስህም ምግብ ነው።
ኑሮህ የሰመረ ይሆን ዘንድ ከሰዎች ሁሉ ጋር ያለህ ግንኙነት ጥንቃቄ አይለየው፤ 
ለጥፋትህም ሆነ ለልማትህ ሰዎች እጅግ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉና በግንኙነትህ ሁሉ ብልህ ሁን።
ብረት ብረትን እንደሚስለው ባልንጀራም ባልንጀራን ይስለዋልና፤
 ጓደኛን በጥንቃቄ በመምረጡ ላይ አትዘንጋ።
ሕይወትህን ለዕምነትህ አስገዛ፤
 በዚህ ትርምስና ሸፍጥ በበዛበት ዓለም
 ምርኩዝ የሚሆንህ ዕምነትህ ብቻ ነው።
ለችግሮች ሁሉ አትረበሽ፤
 የወርቅ ጥራቱ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ አንተም የምትፈተነው በችግር ነውና
የሚደርሱብህን ፈተናዎች ሁሉ ታልፍ ዘንድ ጽኑ ዕምነት ይኑርህ።
በህይወትህ ውስጥ የሚሆኑት ነገሮች ሁሉ የሚጀምሩት፤ 
ፍፃሜህም የሚቀናው በምትወስነው ውሳኔ ስለሆነ ዳተኛ አትሁን።
ዓለም በከፍተኛ ጀብዱ የተሞላችው በታላላቅ ውሳኔዎች ነውና አትፍራ። 
ደግሞም በህይወት ወንዝ ውስጥ እስካለህ ድረስ፤
 ከጥቂት አለቶች ጋር መጋጨትህ ስለማይቀር ተስፋን የሙጥኝ በል።
 እራስህን ንዴት ለተባለው መርዛማ እባብ አሳልፈህ አትስጥ።
ሰላምህን ከሚያውኩ ነገሮች ሁሉ ዞር በል፤ 
ደስታ የሚገኜው ራስህን ለደስተኝነት ባዘጋጀኸው መጠን ነውና
 ብዙ ጊዜህን በደስታ ስራ ላይ አሳልፍ።
ዕለት በዕለት አዕምሮህ ሰላም እየተመገበ መሆኑን አረጋግጥ፤ 
አንተ ያስተሳሰብህ ውጤት ስለሆንክ በተቻለህ ሁሉ በጎ አስብ።
በዚህ የችግር አሜኬላ በሞላበት ምድር በተረጋጋ
 ሁኔታ ለመኖር የሚረዳህ በጎ መሆን ብቻ ነው።
ክፉ ብታስብ በክፉ፤ 
ብጎ ብታስብ በበጎ አስተሳሰብ ዓለምህን ስለምትሰራ
 አስተሳሰብህ ላይ ጥንቃቄ አይጉደል።
ወንዝ ሁሉ ከአንድ መነሻ ነጥብ ተነስቶ፤
 አያሌ መንገዶችን በመቆራረጥ በመጨረሻ የሚደርስበት አንድ የታወቀ መድረሻ ግብ 
እንዳለው ሁሉ አንተም ይኑርህ።
ወንዙ አንዳንዴ የፅናት ጉዞውን የሚያውኩ፤ 
የአወራረድ ስልቱን የሚያደፈርሱ ተለዋዋጭ ሁኔታወች ይገጥሙታል፤
አንዳንዴ በማዕበልና በሀያል ሞገድ ተከቦ እጅ በሚደንቅ ፍጥነት አረፋ እየደፈቀ ሲጎርፍ፤ 
ሌላ ጊዜ ደግሞ እጅግ መንምኖና አቅሙ ተዳክሞ የወትሮው ባልሆነ ፍጥነት ሊያዘግም ይችላል። 
ይሁንና የቱንም ያህል እንቅፋትና መሰናከል ቢገጥመውም
የቱንም ያህል የሀይል፤ 
የፍጥነትና የጊዜ ሚዛን መዋዠቅ ቢያናውጠው ወደ መጨረሻ ግቡ 
የሚያደርገውን የፅናት ጉዞ ከመቀጠል ፈፅሞ አይታቀብም።
ፈፅሞ! ወንዙ ከአንድ ትንሽ ሀይቅ መንጭቶ በሂደት እየገዘፈ
አያሌ መሰናክሎችንና ውጣ ውረዶችን እያለፈ... ሳይበገር፤
እስከ መጨረሻው በፅናት እንደሚጓዘው ሁሉ
አንተም በረጅሙ የህይወት ጉዞ የሚገጥሙህ
 እንቅፋቶችና መሰናክሎች ወደ መጨረሻው ግብህ
ከማምራት ሲገቱህ
በፅናት ከመግፋት ተስፋ ሊያስቆርጡህ አይገባም።
በዚህ ግዙፍ ዓለም ውስጥ በስጋና በደም
በነፍስና በእስትንፋስ የተገለጥክ ህያው ወንዝ ነህና ፍሰትህ የተረጋጋ፤ 
ጉዞህም ሰላማዊ ይሁን።
ይህች ዓለም ያንተ ናትና በአግባቡ አስተዳድራት።

====http://amanuel1979.blogspot.com====

No comments: