March 10, 2010

በፍቅርሽ ታስሬ

የኋሊት ስጎተት በፍቅርሽ ታስሬ፤
ወደፊት መራመድ እያቃተው እግሬ።
አሁንም አሁንም ቆሜ አያለሁ ዙሬ፤ምንም ልቤ ቢፈራ ባይቀር መጠርጠሬ፤
እስከ ዛሬ ድረስ በህይወት መኖሬ፤ተስፋ ሆኖኝ ነበር ፍቅርሽና ፍቅሬ።
ግን እውነት ከሆነ የነገሩኝ ወሬ፤
መኖር አልፈልግም ሞቼ ልደር ዛሬ።
ዱብ እዳ ወድቆብኝ ለሸክሙ አስቸጋሪ፤ ጨንቆኝ ስለፈልፍ እንደ ቀባዣሪ፤
ባንች እምነት የሌለኝ፤ ብመስል ጠርጣሪ፤ መሆንሽን አውቃለሁ ፍቅርሽን አክባሪ።
ቀን እረፍት ሳያምረኝ፤ ወይ ሌሊት ምኝታ፤
እርም ብዬ ትቸ ከሰው ጋር ጨዋታ፤
ስፀልይ፤ ስማለል፤ ከጥዋት እስከ ማታ፤
ያሳየኛል ብዬ ዓይንሽን ለአንድ አፍታ።
መከራ ጠግቤ፤ ደስታ እንድራብበት፤ ሌሎት የበሉትን፤ ዕዳ እንድከፍልበት።
አንጀቴን የበላው፤ አሁን ያሳዘነኝ፤ ታምሜ እማልድነው በሽታ የሆነኝ፤
ሀይለኛው ፍቅርሽ ነው፤ አልረሳም ያለኝ።
እንግዲህ እንተወው ይክተተው ዝምታ፤
ብቻ እንዳትረሽ የፍቅሬን ትዝታ፤ቀን ስትቀመጭ፤ ስትተኝ ማታ።
እንግዲህ ደህና ሁኝ፤ ሁልጊዜ አይለይሽ የእግዚአብሔር ዕርዳታ፤
መከፋት አይንካሽ፤ የልብ ቅሬታ፤ ከለሽበት ሰው ጋር፤ ባለሽበት ቦታ።
እኔ ግን ከእንግዲህ፤ ካንች ከተለየሁ፤ በደስታ እንድትኖሪ እመኝልሻለሁ፤
እስኪጠራኝ ድረስ፤ በህይወት እስካለሁ።

No comments: