May 23, 2018

ተመየጢ ፈላሲት



ተመየጢ ፈላሲት

ይድረስ ለፈላሻዋ- እነሆ እኔ ሐበሻው ነኝ
ቅድመ ፍልሰት- ቅድመ ክህደት ከፍቅርሽ ገፈት ያቀመስሽኝ።
ፈላሻዋ ፍቅሬ ጌጤ የእምዬ ልጅ የእናቴ
?በውኑ ልብሽ ቆርጦ ክዷታል- እማማ ኢትዮጵያን በሞቴ
በለጋ ልቤ ያጠበቅሽው የፍቅር ፈትልሽቅ ቁርኝቱ
ጠብቆብኝ የፍቅርሽ- ፍቅሬ ክረቱ
ደግመሽ በፈለስሽበት ምድር- እስራኤልን በመላ አሰስኩ።
አመሐልኩክን" ብዬ  የእየሩሳሌምን ቆነጃጅት ጠየኩ።" 
ቴል አቪቭ- ጎልጎታ ሳስፈልግሽ ስፈልግ ኖርኩ።
በናዝሬትም- በገሊላም- ፈልጌ  አስፈልጌሽ ነበር፤
በእዝራኤል ሸለቆ አድባር- በሞርያም ተራራ ሥር፤ 
 ዴር ሱልጣን በር ሁሉ ፈልጌ አስፈልጌሽ ነበር።

ግን እስኪ ልጠይቅሽ ያጣሁሽ ፈላሻዋ ፍቅሬ
?ድህነት ኢዘለዓለማዊ መሆኑ አልገባሽም እስከዛሬ
ክደሽ የተውሻት ምድር- እምዬ ኢትዮጵያም
ደሀ አሮጊት ብትሆን እንጂ- በእናትነት አትታማም።
ጥበበኛ እጅሽ ይመስክር- ስንዴዋን ለብርሃንታሽ የጋገረው
አለቷን ለምኩራብሽ የፈለጠው- ዋልካዋን ለሸክላሽ የቆፈረው
?እስኪ ከናዝሬት- ገሊላ ከተመላለሰው ጌታ- አንዴ ልጠይቅሽ ፍቀጂ
ነፍስሽ ከላይ ከራማ
ስጋሽም ከእማማ ኢትዮጵያ አውድማ የተቦካ እንጂ
እስኪ ስለ እውነት መስክሪ- መሬቷን የሳምሻት እስራኤል
?ሆነችልሽ እናት አገር
ያቺ እማማ ያለበሰችሽን ቀሚስ ያቃጠልሽባት ከነዓን
?የምታፈሰው ደም ነው ማር
ያንቺም ቢሆን ያ ያፈቀርኩት ገላሽ ጥቁሩ
?የፍጥረት መቅድምሽ ሥሩ- ጥቁር አይደል ፍሬ ዘሩ
እስኪ በፈጨሽው ጥቁር አፈር- በቀዳሽው ጥር ምንጯ ማይ
ሥጋዬ የተከመረው አጥንቴ የለመለመው ከእማማ ኢትዮጵያ ጤፍ
?ዳጉሳ አይደለም በይ
እንደ ጣና ሳቢሳ በረሽ የሰፈርሽባት ከነዓን
መቼም ጊዜ ደግ ነው ያደረገችውን ሰማን።
ተንቆረቆረ አሉ ደምሽ ቀድታ ፈትሻ ደፋችው
የእኔ አይደለሽም አለችሽ- ይኸው ቁርጡን አወቅሽው።
አንቺ ፍቅሬ ፈላሻዋ መቼም እናትሽ ኢትዮጵያ
ከርዛት ርሃቧ በቀር ላሳር ነው መቼም ላሳር
እናትነት ከሷ ወዲያ
የግሳንግሱ መጠጊያ- እናትነቷስ የጉድ ነው ኢትዮጵያ
ለእምነትሽ- ምኩራቧን ለፍቅርሽ ወጣቷን ሰጥታ- እኔን ልጇን ለግሳሽ
?እናታለም ኢትዮጵያ ከአላት ከቶ ምን ነሳችሽ
ነይ   ተመለሽ   ስሞትልሽ።


ይስማዕከ ወርቁ
 የወንድ ምጥ፡ ፲፱፺፱ ዓ.ም