March 18, 2011

መለየት

የለም! የለም!
መለየት ሞት አይደለም
ሞትም መለየትን አያክለው
መለየትም ሞትን አይመስለው
ትርጓሜያቸው ለየቅል ነው
አንችም እኔም ጅረት ሆነን
ከራሳችን ምንጭ ፈልቀን፤
በራሳችን ፈለግ ፈስሰን
ህይወት በሚሉት መቅበዝበዝ
አገር ምድሩን አዳርሰን
ሄደን! ሄደን! ሄደን! ሄደን!
ወርደን! ወርደን! ወርደን! ሞት በሚሉት ውቅያኖስ
አንድ ስንሆን ተዋህደን
ተገናኜን እንበል እንጂ መች ጨርሰን ተላያየን

የለም! የለም!
መራቅ መለየት አይደለም
ሰው በሰዎች ግዞት
ችግር መከራ ይዞት
አገር ቀዬውን ጥሎ
ስልቻውን በጫንቃው አዝሎ
ቅሉን ጨርቁን አንጠልጥሎ
ብቻውን ሄደ ቢለው ሰፈርተኛው ተጃጅሎ
እርሱ በልቡ ሕንፃ በማይዘመው በማይፈርሰው
ከተጓዘ አኑሮ ሰው
እውን ይኼ መለየት ነው?

የለም! የለም!
መለየት ይህ አይደለም
ትርጓሜያቸውን እንቀይረው
ለአንችና ለእኔ ሌላ ነው
ከፊቴ ቁጭ ብለሽ
ከፊትሽ ቁጭ ብየ
ክንድሽን ካ'ንገቴ ጥለሽ
ክንዴን ካ'ንገትሽ ጥዬ
የምታወሪው ሳይገባኝ
ራሴን ስነቀንቅ
የማወራሽ ሳይገባሽ
ለይስሙላ ጥርስሽ ሲሥቅ
ቻው ቻው ሲለኝ ቀልብሽ
ደህና ሁኚ ሲልሽ ዓይኔ
መለየት ይህ ነው ለኔ።

*'አፍቃሪ' ራስ ወዳድ፤ * ዋ! ያ-ቸርነቷ፤

ለራሴ ህይወት ጎዳና
ለውስጤ ጎዶሎ ሙላት
ሌጣዬ ቢጠነድ ብዬ
ሃዘኔን ቢገባው ብስራት።
ከፅልመቷ ብርቅርቅታ
ከ'ስትንፋሷ ተቋድሼ
ችግር ካዘመማት ጎጆ
አፍቃሪ ልቤን ዳስሼ
ያለችኝን ስወረውር
በሌለኝ እጅ ፍታት ጥሪ
ስስት ካ'ንጀቴ ቢጣባ
መሆን ብከጅል አፍቃሪ
መች እንዳንች ልፍሰስ አልኩኝ
እንደወራጅ ተላትሜ
ያቀረብኩሽ ለራሴ ነው
ቅዠቴን ቢተካው ሕልሜ።
አለያማ ልክ እንደ አዳም
አምላካዊ የወል ክታብ
ከጎድኔ ተሠንጥረሽ
ለባልሽ ልትሆኚኝ 'ርካብ....ልብሽ በክፋት ታውሮ
አይንሽ ካይኔ ሣይነቀል
በማማለል ጥበብ ሾረሽ
ውስጥሽ ላይመዝብኝ ሾተል
ማየት ነበር የ'ኔ ምርጫ
ምግባርሽ ከቃልሽ ሰዶ
እንደ አብርሃም-ይሣቅ ስዌት
ነፍስን ለፈጣሪ ፈቅዶ።


--------------------------
ዋ! ያ-ቸርነቷ

---------------------------
እንቅልፍ አጥቸባት
ላቤ ተንጠፍጥፎ፤ ሥሠሥት ከርሜ፤
ውስጤ ምስሏን አቅፎ፤
እንደ ቃሏ ከንፎ...ያፈቀራት ልቤ፤
ውዳሴው ሊሣካ፤ በስሜት ታውሮ፤
አካሏን ቢነካ፤
የውጥረት ግሳቱ-የስሜት ግለቱ፤
በመፈቃቀድ ወግ-በመዋሰብ ሥልቱ፤....
መለመላ አካሏን ከክንዴ ላይ ጥላ፤
ልክ'ንዳፈቀረ፤ አይኔን-ባይኗ ገላ፤
ሥታልበኝ-ሥግታት፤
ሲጎድል-ሥሞላ፤
እንደ ልጅ ዳስሼ-ሣጎርሳት ሥትበላ፤
ዋ! ያ-ቸርነቷ....
ውለታየ-ከብዷት-ካንገት በላይ ስቃ፤
በያለበት በርታ-በያለበት ደምቃ፤
ከተረፈ 'ካሏ የሠበዝ ቋጠሮ፤
በበራው ከተማ ገላ ተቸርችሮ፤
'ርክሰቱ ንሮ ፈላጊ 'ንዳያጣ፤
አካሏን ሰጠችኝ መታመኗን ሽጣ።
/ካለቀ በኋላ/...ዛሬ-ም'ጣ-ነገ-ም'ጣ፤ አረ 'ንዴት-ይወጣ?

* * *
የማማረጥ አዚም-አቅሏን ጤና ነስቶ
እንደ ዘላን ዕቃ ኮተቷን ኮትቶ
ባ'ንድ ላይወሰን ልቧ ሩቅ ሸፍቶ....
ለስሜቷ ሞቶ - ዋ'ቶ! - ተንከራትቶ
የደከማት 'ለታ....
እንገናኝ ነበር የማታ - የማታ።

ታማኝና እውነተኛ መሆን

"እውነት ፈጽሞ አይወድቅም፤ ሃሰትም ዝንተዓለም አሸናፊ አይሆንም" የተሰኘ መለኮታዊ ሕግ አለ።

በሃሰትና በማጭበርበር ጊዜያዊ እርካታን ማግኘት ይቻል ይሆናል። በመጨረሻ ግን እውነት አሸናፊ ይሆናል።

የእውነት ጀልባ በጥልቁ ባህር መካከል ሊያንገላታት ይችላል፤ ሆኖም አትሰጥምም።

ማንኛውም ሃሰትንና ብልጠትን የተንተራሰ ድርጊት፤ ውጤቱ የሚያነጣጥረው አድራጊው ላይ ነው።

ውጤቱ ሊዘገይ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ግን አይቀሬ ነው።

መልካም ተግባር ሽልማቱን፤ ክፋትም ቅጣቱን ይቀበላሉ።

አበው"ደባ ምሱን፤ ስለት ድግሱን" እንዲሉ፤ ማንም የእጁን/የሥራውን/ውሎ አድሮም ቢሆን ያገኛል።

እርስዎም ከውስጥም ከውጭም ቅንነት ይላበሱ። ሃሳብዎ፤ ቃልዎና አድራጐትዎም ተመሳሳይ ይሁኑ።

የትልቅነት ምልክት እነዚህ ናቸው።ባለንበት ዘመን ብዙዎች ሁለት መልክ አላቸው፤ አንዱ እውነተኛ ሌላው አስመሳይነት ነው።ብዙዎች እውነተኛ ገጽታቸውን ለመደበቅ፤ ሃሰተኛ ጭምብል/ማስክ/ያጠልቃሉ።ስለዚህ ውስጣቸውና ውጫቸው አይገጣጠሙም፤ ማንም እውነትን ግን እስከ መጨረሻው መደበቅ አይችልም።እውነት ራሷን ገሃድ ከመውጣት እንዳትቦዝን የሚያደርጋትን ኃይል የተላበሰች ናት።ለእውነት የሚታገሉትን ሁሉ ፈጣሪ ይረዳቸዋል፤ ስለዚህ ታማኝና እውነተኛ እንሁን።