October 27, 2009

♦ሰው ለሰው♦

==ሰው ለሰው==
ሆድ ሆድን ሲብሰው፤ ሆድ በሆድ ሲከፋ፤ ቀኑ ዘንበል ሲል፤ ዘንበል ሲል ደፋ፤ የሰው ልጅ ለሰው ልጅ፤ ነው አለንኝታ ተስፋ። ጠጋኝ ድጋፍ ሰጪ፤ ወገን አጋር ሲሻ፤ ቅስሙ ስብር ሲል፤ አለሁ ባይ ወጌሻ። ከሕይወት ውዝግብ፤ ከውጣ ውረዱ፤ ከማጣት ከማግኘት፤ ከመጥላት መውደዱ። ከትርምስ ኑሮው፤ ንፋስ ከሚንጠው፤ በማዕበል እንግልት፤ ከሚብጠለጠለው። ጥግ ከለልላ ሆኖ፤ ትንፋሽ የሚያስጥለው፤ ማረፊያ ወደቡ ለሰው ልጅ፤ ያው ሰው ነው።አቋራጭ ሲፈትሽ፤ ኑሮን ለማሸነፍ፤ ጠጠር ቋጥኝ ሆኖ፤ ከእግሩ ሥር ሲወተፍ።ማፍቀር መውደድ ሲሻ፤ ተፈቅሮ ተወዶ፤ ከአፍቃሪ ከወዳጅ፤ ሲደርስ የጥል መርዶ።ቀኑ ጭልም ሲል፤ ፀሐይ በጧት ወጥታ፤ሊስም የቀረበ፤ በጥፊ ሲመታ። ልብን ሲቃ ይዟት፤ ዓይን እንባ ሲያዘራ፤ ከሰው ወዲያ ለሰው፤ ማን አለ እሚራራ?ማን አለው ለሰው ልጅ፤ ከሰው ወዲያ ለሰው፤በአዘን በደስታ፤ በሁሉ ሚደርሰው፤ ሲስቅ አብሮት ስቆ፤ አንባ አባሹ ለሰው። ነው ውሉ ሰው ለሰው፤ ሰው ከሰው፤ ሰው በሰው፤ አቻ አጋርም የለው፤ ከሰው ወዲያ ለሰው። ሰው ለሰው ነው ጌጡ፤ ሰው ለሰው ነው ክብሩ፤ ሰው ለሰው ነው ተስፋው፤ ሰው ለሰው ነው ፍቅሩ፤የኑሮው ዋስትና፤ ዋልታና ማገሩ።
----------------------------
ትዕግስት ህሩይ፤ መስከረም 05/1991